ሳድግ ተረት እየተነገረኝ ቁመቴ ጨመረ


ሳድግ ተረት እየተነገረኝ
ቁመቴ ጨመረ…ደረቴ አጦተ…ዳሌዬ ሰፋ….
ተረቱ ምን ነበር…?
“ትምህርቱን በርትቶ ያጠና ልጅ ዶክተር ይሆናል…ስታድጊ ፓይለት ነው የምትሆኝው…አቤት ከዛ ሀብታም ትሆኛለሽ …”
ይሄ ከቡርዧ የተዳቀለ ካፒታሊዝም ከ10 አመት በሁዋላ የተማረውን አፈር ሊከተው እንደሚችል የሚያይ ንቃተ ህሊና አልነበራቸውም …. እናትና አባቴ
.
.
ሌላ ተረት ደግሞ
“ፀልዪና ብዪ…የበላሽውን ከስጋሽ እንዲቀላቅለው…” ይሉኛል…ጉሮሮ እየፋቀ የሚወርደው ቂጣ ግን በፀሎትም ሆነ በግዝት ሊያፋፋኝ አልቻለም…
ልክ 12 አመቴን ስደፍን እናትና አባቴ በሽታ አልጋ ላይ ጣላቸው…እንደ ጦር ቁስለኛ ውሃ የሚያዥ ቁስላቸውን እያጠብኩ ጎረቤት የሚያዘውን ባህላዊና መንፈሳዊ ህክምና ሞከርኩላቸው…
አልሆነም.. .
ሞቱ…
የህፃናት ማሳደጊያ ገባሁ…
ብዙም ሳይቆይ ሰውነቴ መቁሰል ጀመረ…
ህክምና ተደረገልኝ…ህመሜ ኤች.አይ.ቪ ነበር.. .
ዩንቨርሲቲ ስገባ መድሀኒት መውሰድ ጀመርኩ…ደግነቱ የኔ ትውልድ አንዴ ፖስት ፒል ሌላ ጊዜ ደሞ ወሊድ መከላከያ እንክብል ወሳጅ ሰለነበር በሌላ ብልቃጥ ውስጥ የገለበጥኩትን የእድሜ ማራዘሚያ መድሀኒት ድንገት እንኳን ስውጥ ብታይ ማንም ሳይጠረጥር ጥሩ ነጥብ ይዤ ተመረቅኩ።
ስራ ፍለጋ ብዙም ሳልንከራተት አንድ አሪፍ ቦታ በሚገርም ደሞዝ ልቀጠር ሁኔታዎች ተመቻቹ… “ይህን ስራ ካገፕሁ መጀመሪያ መሽተት የጀመረው የቻይና ጫማዬን እቀይረዋለሁ … አይደለም…አይደለም… የሚጥም ምግብ እበላበታለሁ…አይ መጀመሪያ ቤት መከራየት ይቀድማል…” ብዙ አሰብኩ…ፈተናውን አልፌ ለቃለ መጠይቅ ስጠራ የለበስኩት ልብስ በሙላጭ ሳሙና የታጠበ መናኛ ቀሚስ ነበር…ጫማዬ ፈታኞቹን እንዳይሸታቸው ተሳቀቅኩ…
አለቅየው ግን ጭንቅላቴን ብቻ ሳይሆን ጭኔንም መፈተን ፈለገ…
የሚሸት ጫማዬን ከአልጋው ስር ወርውሬ ከሆቴሉ አልጋ ላይ ወጣሁ…ድንግል መሆኔ አጓጉቶት እራቁቱን ወጣብኝ … ከጥቂት ደቃዎች በሁዋላ ንፅህናዬን ለመመስከር ከፈሰሰው ደም ላይ የድርሻውን መቅሰፍት ወሰደ…
ሁለት አመት አለፈ….
ድህነቴን ተሰናበትኩት….
አማረብኝ…
አለቃዬ ሞተ…ገረመኝ … በጭኖቿ መሀል ሰይፍ እንዳላት ጣኦት የምታመም እንጂ የምሞት እንዳልሆንኩ ተገለጠልኝ…እናም እንደ ጣኦትነቴ በሽታዬ ደባል እንጂ አጥቂ አልመስል አለ…እኔን ያወጡ “ካልከካሁሽ እድገት አታገኚም” ያሉኝ ሌሎች ሁለት አለቆችም ሰይፉ በላቸው…
እንደ አጋጣሚ ሶስቱም አንድ ቤተ ክርስቲያን ተቀበሩ… ጫማዋ የሚሸት ጣኦት መሆኔን አላወቁም ነበርና አፈር በሉ…ሁሌ ቅዳሜ ጠዋት ዝንጥ ብዬ እሄድና ሀውልታቸውን እያየሁ እስቃለሁ…አሁን ከሞት ባላስነሳም የምገድል አምላክ ሆኛለሁ…
እናም ተረት ተረቶች ትዝ ይሉኛል…
.
.
ድንገት ስለ ሴቶች መብት እታገላለሁ የምትል ቡርዧ ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ሴት ስለችግሩ ጥልቀት በተሞላቀቀ አክሰንት ቲቪ ላይ ስትደሰኩር ስሰማ ብልጭ ይልብኝና እሳደባለሁ…
“እናትሽን!!!!”

አስተያየቶን እዚህ ይተዉልን

Blog at WordPress.com.

Up ↑